ማቴዎስ ወንጌሉን የሚጽፍልን ኢየሱስን ንጉሡ-መሲሕ እንደሆነ እንድናስብ በሚያደርግ መንገድ ነው:: ገና በወንጌሉ ጅማሬ ላይ “የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ” በሚል መግቢይ ሰፊውን ዘገባ ይጀምራል:: ኢየሱስ እንዴት የአብርሃምና የዳዊት ልጅ እደሆነ ይተርክልናል:: ቀጥሎም የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን በተደጋጋሚ በመጥቀስ መወለዱ እንዴት የትንቢቶቹ ፍፃሜ እንደሆነም ያስረዳል:: በዚህ በክርስቶስ ልደት ታሪክ ውስጥ ግን ኹለት ቀልብን የሚገዙ አካላት በንጽጽር ቀርበዋል:: አንደኛው ንጉሡ ሄሮድስ ሲሆን በሌላኛው ወገን የምናገኛቸው ደግሞ ከምሥራቅ የመጡት ጠቢባን ወይም ሰብዓ ሰገል ናቸው::
ንጉሥ ሄሮድስ
ንጉሥ ሄሮድስ በትውልዱ ኤዶማዊ ሲሆን ከ37 ዓ.ዓ እስከ 04 ዓ.ም ድረስ በአውግስጦስ ቄሳር መንግሥት ሥር አይሁድን የገዛ ንጉሥ ነበር:: መጠሪያውም “የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ነበር:: ነገር ግን ሄሮድስ እጅግ በጣም ጨካኝ እና አረመኔ ሰው ነበር:: አንዳንድ የታሪክ ጸሓፍት እንደሚናገሩትም መንግሥቴን ይነጥቁኛል በሚል ፍርሃት የገዛ ሚስቱን እና ሁለት ልጆቹን የገደለ ክፉ መሪ ነበር:: በህይወቱ የመጨረሻ ጊዜያት በኢየሩሳሌም የነበሩ ብዙ ምሁሮች: ባለስልጣናት እና የተከበሩ ሰዎችን ሰብስቦ እንዲሰለቡ ያደረገ ሲሆን: ወደ ሞት አፋፍ በተጠጋም ጊዜ: በሙሉ እንዲገደሉ ያደረገ ንጉሥ ነበር:: እና ይህ ሄሮድስ ስለ ኢየሱስ መወለድ ሲሰማ የሚከተሉትን ነገሮች አደረገ::
ደነገጠ – “ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፥ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር” የማቴዎስ ወንጌል 2:3 – የጠቢባኑን ጥያቄ ሲሰማ ታወከ:: ተረበሸ:: እርሱ ከንግሥና ዙፋኑ ሳይወርድ ሌላ ንጉሥ መወለዱ አስጨነቀው:: ግራ አጋባው:: መንግሥቱ እና ስልጣኑን የሚነጥቀው ንጉሥ እንደመጣበት በማሰብ ተደናገጠ:: ሄሮድስ ያልገባው አንድ ነገር ግን: ይህ በከብቶች በረት የተወለደ የዓለም ንጉሥ መንግሥቱ ከዚህ ዓለም አይደለችም::
ጠየቀ – “የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው።” የማቴዎስ ወንጌል 2:4 ሄሮድስ ከእነዚህ ሰዎች አንድ ነገር አውቋል:: መጻህፍት እንደሚናገሩት ክርስቶስ የሚወለደው በቤተልሄም ይሁዳ ነው:: ንጉሡ ሄሮድስ በዚህ ብቻ አልቆመም:: የካህናት አለቆችንና ጸሐፍትን ብቻ ሳይሆን ሰብዓ ሰገልንም ጠርቶ ወደ ቤተልሄም በመላክ ስለ ህፃኑ በሚገባ እንዲመረምሩ አዘዛቸው::
ለማታለልም ምከረ – “ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ሰድዶ። ሂዱ፥ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ አላቸው።” የማቴዎስ ወንጌል 2:8
ሰብዓ ሰገል እንደተሣለቁበት ባየ ጊዜ ብስጭቱን የገለጸው ምንም የማያውቁ ህፃናትን በመጨፍጨፍ ነው:: “ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ ተሣለቁበት ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጣና ልኮ ከሰብአ ሰገል እንደ ተረዳው ዘመን በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን፥ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ።” የማቴዎስ ወንጌል 2:16
ሰብዓ ሰገል
የእነዚህ ሰዎች ታሪክ እና አመጣጥ ከምስራቃዊ ቀደምት መንግሥት ከፋርስ እና ሜዶን ጋር የተቆራኘ ነው:: በጥንት ዘመን እደዚህ አይነት ሰዎች በባሎን ይኖሩ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱሳችን ይነግረናል:: ሰብአ ሰገል ወይም “ጠቢባን” በጥንት ዘመን የንጉሥ አማካሪዎች የነበሩ ናቸው። በዘመኑ የተማሩና አስተዋዮች ነበሩ። ነገሥታት ወደ ዙፋን እንዲመጡ የሚያደርጉም ነበሩ:: አንዳንድ ጊዜም ከኮኮብ ቀጠራ እና ከጥንቆላ ጋር የተገናኙ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታሰባል:: (ዳን. 2:1-10፤ የሐዋርያት ሥራ 8:9-24 ይመልከቱ) ቅዱሳት መጻሕፍት ኮከብ ቆጠራን ይከለክላሉ (ኤር. 8:2፤ 19:13፤ ኢሳ. 47:13-15):: በዚህ ክፍል እንደምንመለከተው ግን እነዚህ ጠቢቢባን ባህሪያቸውና ክህሎታቸው ምንም ይሁን ምን፣: የተወለደውን የአይሁድ ንጉሥ ያወቁት በቤተ-መንግሥት የነበሩት ባለስልጣናት ሳይሆኑ በሩቅ ያሉት ኮኮብ ቆጣሪዎች መሆናቸውን ነው:: እነዚህ ሰብዓ ሰገል ስለ ኢየሱስ ሲሰሙ ከሄሮድስ በተቃራኒ መንገድ የሚከተሉትን ነገሮች አደረጉ::
ከምሥራቅ እስከ ኢየሩሳሌም መጡ:: የተወለደውን ህፃን ለማየት የቀናት: ምናልባትም የሳምንታት ጉዞ አድርገው መጡ:: ይህ የተወለደው ንጉሥ ከዓለም ነገሥታት ሁሉ ይበልጣል:: “ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው። ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት” የማቴዎስ ወንጌል 2:10-11
በእናቱ እቅፍ ያለው ህፃን የሚሰገድለት ንጉሥ ነው:: “proskuneo” የሚለው የግሪክ ቃል ይህ ስግደት ለሌሎች ነገሥታት ከሚደረጉ ስግደቶች ጋር አንድ አለመሆኑን ይነግረናል:: ይህ “proskuneo” የሚለው ቃል ለመለኮት ብቻ የሚደረግን ስግደት የሚያሳይ ነው:: ስለዚህ በእናቱ እቅፍ ላይ ያለው ልጅ የሚሰገድለት አምላክ ነው:: ይህንን ቃል በሌላ የአዲስ ኪዳን ክፍል ላይ የምናገኘው በማቴዎስ ወንጌል 4:10 ላይ ነው:: ጌታ ኢየሱስ በምድረ በዳ በድያብሎስ በተፈተነበት ወቅት: ወደ ተራራ ጫፍ አውጥቶት የዓለምን ክብር ሁሉ ካሳየው በኃላ ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህንን ሁሉ ክብር እሰጥሀለው” አለው:: ጌታ ኢየሱስ ግን “ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ብቻ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ” በማለት መልሶለታል::
በመቀጠል እነዚህ ጠቢባን ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት። ይህ በብዙ ባህሎች ውስጥ የሚገኝ ጥንታዊ ልምድ ሲሆን: ለንጉሡ መገዛትን የሚያመለክት ነው:: “ወርቅ” የተለመደ የስጦታ አይነት ነው:: በመቀጠል ደግሞ የሰጡት “ዕጣን” ነው:: ይህ ከአይሁድ የክህነት ስርዓት ጋር የተገናኘ ነው:: መስዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ መልካም መዓዛው ወደ እግዚአብሔር የሚያርግበት መንገድ ነው:: ይህ ስጦታ የሚያሳየን የተወለደው ህፃን ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ሊቀ-ካህንነቱንም ጭምር ነው:: ትንሽ ግራ የሚያጋባው ሦስተኛው ስጦታ ሲሆን እርሱም “ከርቤ” ነው:: ከርቤ በዚያን ዘመን ጥቅም ላይ የሚውለው በዋናነት ሬሳ ለማድረቅ ነበር:: ይህ ለተወለደ ህፃንም ሆነ ለንጉሥ የሚሰጥ አይነት አይደለም:: ነገር ግን ይህ ድርጊት ትንቢታዊ ነው:: የክርስቶስን መስዋዕታዊ ሞት የሚያመለክት ነው:: ህፃኑ ንጉሥ: ሊቀ-ካህን ብቻ ሳይሆን ስለ ዓለም ኃጢአት የሚሞትም አዳኝ ነው:: በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ መልዓኩ ለዮሴፍ “ማርያም ከመንፈስ ቅዱስ የፀነሰችው የሚወለደው ልጅ ህዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል” በማለት ነግሮታል:: ጥያቄው “እንዴት ነው የሚያድናቸው?” የሚለው ነው:: በብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደገለጠው መሲሑ መከራ እንደሚቀበል እንደሚሞት እና እንደሚነሳ የታወቀ ነው:: “በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው። ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፥ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል።” (የሉቃስ ወንጌል 24:45-47)
ስለዚህ የምናከብረው የልደት በዓል የማንኛውም ህፃን ልጅ ልደት አይነት አይደለም:: ይልቁንም የምናከብረው በበረት የተወለደውን: ፍፁም ህይወት በመኖር የእግዚአብሔርን ጽድቅ በሙሉ የፈጸመውን: በምትካዊ ሞቱ ከእግዚአብሔር ጋር ያስታረቀንን: በትንሳኤው አዲስ ህይወት እና ታላቅ ተስፋ ያመጣልንን ንጉሣችንን: አምላካችንን እና ሊቀ-ካህናችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው:: ስለዚህ ይህንን ጊዜ ስናስብ እንደ ሰብዓ ሰገል በታላቅ ደስታ: ለኢየሱስ በመገዛት: በስግደት እና በአምልኮ ሊሆን ይገባል:: ይህንንም ታላቅ የምሥራች ለሌሎች በማካፈል ሊሆን ይገባል::
ጸሓፊ፡ ዮናስ ደመቀ